የደቡብ ኦሞው አርማ - ላሌ ላቡኮ፤ ከእረኝነት እስከ ሰብዓዊ ተቆርቋሪነት
የደቡብ ኦሞው አርማ - ላሌ ላቡኮ፤ ከእረኝነት እስከ ሰብዓዊ ተቆርቋሪነት
*******************
ከደቡብ ኦሞ ካራ ዱዝ እስከ ዲበከም ፣ ከአሜሪካ እስከ ጂንካ ደማቅ የሰብአዊ ህይወት ጉዞን በማጣቀስ ተምሳሌትነቱን የምንዘክረው የዛሬው ጀግና ላሌ ላቡኮ ነው።
ላሌ ላቡኮ በካራ ብሔረሰብ ውስጥ ከሁለት ሺ በላይ ህዝብ የማይኖርባት አነስተኛ መንደር ውስጥ ነው የተወለደው። የኦሞ ቻይልድ ግብረ ሰናይ ድርጅት መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ ላሌ ላቡኮ ዘጠኝ ዓመት እስኪሞላው የልጅነት ጊዜውን ያሳለፈው በእረኝነት ነው።
በእነሱ መንደርም ሆነ በአጎራባች መንደሮች ልብስ አይታወቅም። አዋቂ ወንዶች በከፊል የሚለብሱ ሲሆን ሴቶች ከፊት ለፊታቸው ብቻ ትንሽ እራፊ ጨርቅ አልያም ቆዳ ብቻ ነበር የሚያገለድሙት። ልጆች ደግሞ ምን አልባት ለመኝታ ከቆዳ የተዘጋጀ እንደ ብርድ ልብስ የሚገለገሉበትን ከመልበስ ውጭ ሁሌም ራቁታቸውን ነው የሚውሉት። ላሌም የስድስት ዓመት ልጅ እያለ የቤተሰቡ ከብቶች ያድሩበት ወደነበረው ራቅ ያለ ጫካ እየሄደ ከአባቱ ጋር ከብቶችን እየጠበቀ ያድራል። በአካባቢው እንደ ቆርኪ ያሉትን የዱር እንስሳት በጦርና በቀስት ማደን የተለመደ ቢሆንም የላሌ አባት መሳሪያ ስለነበራቸው ይዘውት ሄደው እሳቸው በጥይት ትልልቆቹን ሲያድኑ እሱም በዱላ በመታገዝ ግልግሎቹን ይይዛል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ በ2012 ዓ.ም የካቲት 13 ዕትሙ የላሌን ውጣ ውረድ ባስነበበበት መጣጥፉ የልጅነት ዘመኑ በጀመረው መስመር አለመቀጠሉን ያስታውሰናል። አንድ ቀን የእሱንም፤ የቤተሰቡንም ከዛም አልፎ የብዙዎችን ሰቆቃ የሚታደግበት አጋጣሚ እንደተፈጠረ በማሳያነት በማቅረብ። ላሌ አጋጣሚውን እንዲህ ያስታውሰዋል «በአካባቢው ትምህርት ቤት አልነበረም፤ ወደ አካባቢው ለመጀመሪያ ግዜ የመጡት የስዊድን ሚስዮናውያን ነበሩ። ፈረንጅ ልጆችን ይዞ ይጠፋል ተብሎ ስለሚፈራ የአካባቢያችን ሰው ልጆቹን ትምህርት ቤት አይልክም። አባቴ ነገሮችን እንዴት እንደተረዳ ባላውቅም እኔ ትምህርት ቤት እንድሄድ ፈቀደ። እናም ከትውልድ መንደሬ ስልሳ ኪሎ ሜትር ርቀት በኬንያና በኢትዮጵያ ድንበር ላይ ወዳለች ‘ትውሽ’ ወደ ምትባል አንዲት መንደር በማቅናት ትምህርት ቤት ገባሁ። መንገዱ ረጅም ስለነበር ወደ ቤተሰብ የምመጣው በየሶስት ወሩ ነው። በዚያ የሚስዮናውያን ትምህርት ቤትም በስንዴ መቋጠሪያ ማዳበሪያ ላይ እየተኛሁ፤ ቁርስም፣ ምሳና ራትም የስንዴ ንፍሮ እየበላሁ ከአንድኛ እስከ አምስተኛ ክፍል ተማርኩ። አጠቃላይ የነበርነው ተማሪዎች ከስልሳ አንበልጥም። ከዚሁም በተለያዩ ምክንያቶች የሚያቋርጡ ነበሩ እኔ ግን ትምህርቴን ቀጠልኩ» ይላል ላሌ።
ዛሬ ላይ 40ዎቹ መጀመሪያ ላይ ወደ ጎልማሳነት የእድሜ ክልል የተሸጋገራ ላሌ ከትምህርት ህይወቱ ባለፈ ዛሬ ድረስ ዓለም አቀፍ እውቅናን እንዲቸረው ያደረገውን አጋጣሚንም ጋዜጣው ያስታውሰናል። «የአስራ አምስት ዓመት ልጅ እያለሁ እንደተለመደው ሶስት ወሬን ጠብቄ የቤተሰቤን ናፍቆት ለመወጣት ወደ ትውልድ መንደሬ አቀናሁ። እዛም እያለሁ አንድ ጧት ሰፈር ውስጥ በእግሬ ስንሸራሸር አንድ የሚያስደነግጠኝ አጋጣሚ ተፈጠረ። አምስት የሚደርሱ የሰፈሩ ሽማግሌዎች ከአንዲት እናት ላይ ያቀፈችውን ልጅ በጉልበት ይነጥቋታል። ልጇን የምትነጠቀው እናት ለቅሶና ሰቆቃ ደግሞ እኔን እግሬን ከእርምጃ ገትቶ ትኩረቴን እነሱ ላይ እንዳደርግ ያስገድደኝ እና ነገሩን መከታተል እጀምራለሁ። ሽማግሌዎቹ ህጻኑን ይዘው ‘ሚንጊ ፣ሚንጊ!’ እያሉ መሮጥ ይጀምራሉ። እናትም ልጇን ለማዳን እያነባች ትከተላለች። እኔ ደግሞ የሚሆነውን ለማየት ተደብቄ ሁሉንም እከተላቸዋለሁ። በመጨረሻ ተደብቄ እያየኋቸው ሽማግሌዎቹ ጫካ ውስጥ በመግባት ያንጠለጠሉትን ህጻን ወንዝ ውስጥ ይጨምሩታል። እናትየዋንም፣ ህጻኑንም አላውቃቸውም። ነገር ግን የተፈጠረው ነገር ክፉኛ ስላሳዘነኝ በተደበቅኩበት ሆኜ አለቅሳለሁ። ወዲያውኑም ለምን ስል ራሴን ብጠይቅም መልስ ማግኘት ስላልቻልኩ አዕምሮዬ ቢያርፍ ብዬ ወደ ቤት በመመለስ ጥያቄውን ለእናቴ አቀረብኩላት። እናቴ ጥያቄዬን ለመመለስ ፈርታ ዝም አለችኝ። ነገሩ በጣም ስላሳዘነኝ እናቴ መልሱን ካልሰጠችኝ ወደ ትምህርት ቤት ስሄድ በዛው እንደምጠፋ ነገርኳት። እናቴም ነገሩን ለማንም እንደማላወራ ቃል ካስገባችኝና ካስጠነቀቀችኝ በኋላ በአካባቢው ያለውንና የብዙ ህጻናትን ህይወት እየቀጠፈ የኖረውን ጎጂ ልማድ ከስር መሰረቱ ገላልጣ ነገረችኝ» ይላል፡፡
በደቡብ ኦሞ ዞን ከሚገኙት አስራ ስድስት ብሄር ብሄረሰቦች መካከል በካራ፤ ሀመርና በና ብሄረሰቦች "ሚንጊ" የሚባል ባህል አለ። በዚህ ባህል መሰረት ህጻናት ቀድመው ጥርስ ማብቀል ያለባቸው ከስር ወይም ከታች ነው ተብሎ ይታመናል። ስለዚህም አንድ ህጻን ዘጠኝ ወር ሳይሆነው ቀድሞ በላይኛው ድዱ ጥርስ ካበቀለ ወይንም እስከ ሰባት ዓመቱ ወድቆም ቢሆን የላይኛው ጥርሱ ከተሰበረና ከወለቀ "ሚንጊ" ይባላል። ያገባች ሴትም ነገሮች በባህሉ መሰረት ቡናና ማር ተይዞ ምርቃት ሳይከናወን ብታረግዝ "ሚንጊ" ይባላል። አንዲት ሴት ልጃገረድ ሆናም ሳታገባ ካረገዘች ሚንጊ ይባላል። እነዚህ ሶስቱ ነገሮች ከተፈጠሩ በህብረተሰቡ ዘንድ በሞት ያስቀጣሉ። "ሚንጊ" ማለት እርግማን ነው ፡፡እነዚህ ልጆች ካልተገደሉ "ድርቅ ይመጣል፤ ዝናብ ይቆማል፤ በሽታ ይገባል፤ ቸነፈር ይመታናል፤በአጠቃላይ ክፉ መንፈስ መጥቶ ህዝብ ያልቃል" ብለው ያምናሉ።
ስለዚህ ህጻናቱ አንድም ወንዝ ይጨመራሉ፤ አልያም ከገደል ይወረወራሉ፤ ካልሆነም ጫካ ወይም ዋሻ ውስጥ አውሬ እንዲበላቸው ይጣላሉ። ላሌም ያኔ ሽማግሌዎቹ ወንዝ ውስጥ ጥለው የገደሉት ልጅም በዚሁ መንገድ መሆኑ መረዳቱንና ይባስ ብሎም ሁለት ታላላቅ እህቶቹን በተመመሳሳይ መንገድ ማጣቱን ለመጀመሪያ ጊዜ ከእናቱ መስማቱ ክፉኛ አሳዝኖታል።
ላሌ ላቡኮ ባየውም፤ በሰማውም ነገር ውስጡ ክፉኛ ቆስሎ ስለነበር እናቱ የነገረችውን ታሪክ ሰምቶ ከመቀበልም ይልቅ ነገሩን ለመጋፈጥ ይወስናል። ከዓመታት በኋላም ትምህርቱን አጠናቆ ወደ መንደሩ ሲመለስ "መንጊ" በሚል የሚጣሉትን ህጻናት ለማሳደግ ይወስናል። እናት ሀሳቡን ስትሰማ መጀመሪያ "ባህል ነው ተው "ብላ ተከራክራ ነበር። በኋላ ግን ነገሩን ሲጀምረው ደግሞ እሱና ቤተሰቡ ላይ ችግር እንዳይፈጠር ስጋት ላይ ጥሏታል። እሱ ግን በነገሩ ቀጥሎበት በይፋ «እኔ ጫካ፤ ወንዝና ገደል ልሁንና ለእኔ ስጡኝ እርግማኑንም እኔ ልውሰድ» ብሎ ሽማግሌዎቹን ይጠይቃል። በእውነትም እናቱ እንደሰጋችው ማህበረሰቡ ነገሩን በቀላል አልተቀበለውም። ይልቁንም ከላሌም ጋር ሆነ ከቤተሰቡ ጋር ቡና ላለመጠጣት በመወሰን ቤተሰቡን «ሚንጊ ነው ከእነሱ ጋር የበላና የጠጣ ይረገማል፣ ይሞታል» በማለት ማግለል ይጀምራሉ። በዚህም አላቆሙ፤ ከመንደሯና ከአካባቢው ለማባረር አስበው የአባቱን ቤትና ሙሉ ንብረት ለማውደምም ይዘጋጃሉ፤ ይነጋገራሉ ነገር ግን ሁሉም ሳይሳካላቸው ይቀራል።
ላሌ በውሳኔው በመጽናት ስራውን ይቀጥላል።ነገር ግን ሀሳቡን የሚቀበልና የሚስማማ በመጥፋቱ እሱ በግሉ ህጻናቱ ሊገደሉ ነው የሚል ወሬ ሲሰማ ቢሮጥም የሚደርሰው ልጆቹ ከተገደሉ በኋላ ነው። እናም አንድ ልጅ ለማዳን አንድ ዓመት ይወስድበታል። በዚህ ጊዜ ቤተሰብን ከመምከርና በግልም ከመሮጥ ባለፈ ሌላ ነገር መስራት እንዳለበት ይገነዘብና ፕሮጀክት ቀርጾ መንቀሳቀስ ይጀምራል።
ፕሮጀክቱም የተስፋ ጭላንጭልን ይዞለት መጣ። ሆኖም ህጻናቱን ከሞት ይታደግልኛል ብሎ የቀረጸው ፕሮጀክት ስድስት ልጆችን ከሞት ካተረፈ በኋላ እንዲህ ማድረግ አትችልም» በማለት በተጠናከረ መልኩ ይከለክሉታል። በዚህ ወቅትም በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ አስራ አንድ ልጆች "ሚንጊ" ተብለው እንዲሞቱ ተፈርዶባቸዋል። በሌላ በኩል ለእሱ ድጋፋቸውን የሚሰጡት ወጣቶች ቁጥር ደግሞ ከቀን ወደቀን እየጨመረ ስለነበር እነሱ ላይ ትኩረቱን አድርጎ መስራቱን ይቀጥላል። ወጣቶቹ መንጊ ተብለው የሚገደሉትን ህጻናት መሰብሰባቸው ከታወቀ እርምጃ ሊወሰድባቸው ስለሚችል ከሌሊቱ አስር ሰዓት ጀምሮ በድብቅ እስከ ንጋት ነበር የሚሰበሰቡት።
የላሌ ላቡኮ ለዓመታት የለፋበት ጥረቱና ድካሙ ወንዝ ተሻግሮ ተጽዕኖ ፈጥሯል፣ፍሬም አሳይቷል፡፡
👉ከ12 ዓመታት ጥረትና ትምህርት በኋላ በካራ "ሚንጊ" የሚባለው ጎጂ ልማድ ሙሉ ለሙሉ ቀርቷል።
👉በሀመር እስከ ሰባ በመቶ ቀንሷል ።
👉ቀደም ሲል በዓመት ከ300 እስከ 400 የሚደርሱ ህጻናት ይገደላሉ። ዛሬም ሀመር ውስጥ "ሚንጊ" በሚል የሚገደሉ ህጻናት አሉ። ሆኖም በዓመት ከ20 እና ከ30 አይበልጡም ሲል ለውጥ መኖሩን ላሌ አሳይቷል።
👉ላሌ ልጆቹ ነጻነታቸውን እንዲያገኙ በማሰብ አድገው ተምረው ራሳቸውን ሲችሉ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የማስታረቅ ስራ ይሰራል።
👉 ላሌ ይሄን ስራ ከባለቤቱ ጋር አንድ ልጅ ከወለዱ በኋላ ቤቱ የጀመረው የግል እርዳታ ድርጅት ፈቃድ እስኪያገኝ ድረስ ልጆቹ ያደጉት እሱ ጋር ነበር።
👉“ሚንጊ” ተብለው የሚጣሉ ህፃናት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራው የኦሞ ቻይልድ ከተመሰረተ ከ13 ዓመታትን አስቆጥሯል።
👉እስከ ቅርብ ጊዜም ሀምሳ ልጆችን በቤት ኪራይ ሲያሳድግ ቆይቷል።
👉አሁን ላይ ከደቡብ ኦሞ ዞን መንግስት በሰጠው ቦታ ላይ የህጻናት ማሳደጊያ፣ ትምህርት ቤትና መመገቢያ ቦታ እየገነባ ይገኛል።
👉የኦሞ ቻይልድ ግብረሰናይ ድርጅቱ ለለበርካታ ዜጎች የስራ እድል ፈጥሯል።
👉ላሌ ልጆቹንም የሚያየው እንደሞቱ እህቶቹ ነው። ላሌ ታናሽ እህትና ወንድሞቹንም በበሽታ አልቀውበታል። እናም "ሚንጊ" የተባለው ጎጂ ልማዳዊ ድርጊትና በሽታ ለእሱ ቀዳሚ ጠላቶቹ ናቸው።
👉በአሁኑ ጊዜም ላሌ በሀመር፣ ካራናና በና አካባቢዎች የትምህርት ቁሳቁሶችን ለተማሪዎች ያቀርባል፤ የተጎዱ ትምህርት ቤቶች እንዲታደሱ ያደርጋል። ዛሬም ችግሩ ሙሉ ለሙሉ ባለመቀረፉ ከመንግስት ጋር በመሆን ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ይሰጣል። በቅርቡም በአካባቢው ትምህርት ቤት ለማቋቋም አስቦ ግንባታ በማከናወን ላይ ይገኛል።
👉 ላሌ በመምህርነት ከተመረቀ በኋላ በጀርመን በመንፈሳዊ ትምህርት፤ በአሜሪካ በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪውን ይዟል።
👉ናሺናል ጂኦግራፊ በስራው ዕውቅና ሰጥቶ ሸልሞታል
👉የኒዮርክ ሎዋል ቶማስ አዋርድ ተሸላሚም ነው፡፡
👉የዓመቱ በጎ ሰው ተብሎ ለመሸለም የበቃ ሲሆን በእሱ ስራ ላይ የሚያጠነጥነው «ኦሞ ቻይልድ ዘሪቨር ኤንድ ቡሽ» የሚለው ፊልምም በርካታ ሽልማቶችን አስገኝቶለታል።
👉በርካታ የህወት ዉጣውረዶቹን ጭምር በዓለም ተጽዕኖ ፈጣሪዎች በሚቀርቡበት ቴዴክስ ቶክ /TEDx Talks/ ቀርቦ ልምዱን አጋርቷል፡፡
ለዚህ ሁሉ ከፈጣሪ ቀጥሎ መማሬ ጠቅሞኛል የሚለው ላሌ ፣ከምንም በፊት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ጨምሮ የትኛውንም ማህበራዊ ችግር ለመቅረፍ መማር እንደሚገባ ይመክራል። ለዚህም በተለይ እሱ እንደተወለደበት አካባቢ በርካታ ማህበራዊ ችግሮች ባሉበትና ትምህርት ባልተስፋፋበት አካባቢ መንግስትም ሆነ እርዳታ አድራጊዎች ከሁሉም በፊት ትምህርት ላይ ትኩረት በማድረግ የአቅማቸውን መስራት እንደሚጠበቅባቸው ያስገነዝባል።
(በኢቢሲ ሳይበር ሚዲያ፤ሰኔ 23፣2014)